Wednesday, January 25, 2012

ምጽዋት - እዉነተኛዉ የተፈጥሮ ሚዛን

ዲ/ብርሃኑ አድማስ እንደጻፈው




አንድ ገዳም ዉስጥ የሚኖሩ አንድ አባት አዉቃለሁ፡፡ እኝህ አባት ሁል ጊዜ የሚናገሩት በምሳሌና በተዘዋዋሪ ነዉ፡፡ በዚህ ምክንያት ለእርሳቸዉ እንግዳ የሆነ ሰዉ ነገራቸዉን ቶሎ ላይረዳዉ ይችላል፡፡ በአንድ ወቅት ከጓደኛየ ጋር ሆነን ስለ ምጽዋት ስናነጋግራቸዉ በአሁኑ ጊዜ ከጠቃሚነቱ ይልቅ ጎጂነቱ ያመዝናል የሚለዉ ሰዉ እንደሚበዛና በርግጥም ይህን ሊያስብሉ የሚችሉ ብዙ አጭበርባሪዎች መኖራቸዉን ነገርናቸዉ፡፡ እርሳቸዉም ዝም ብለዉ ካደመጡን በኋላ የሚከተለዉን ታሪክ ነገሩን፡፡ በንጉሡ ጊዜ ፈረንጆች መጥተዉ አንድ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ጥያቄዉም ጥቁር ነገር ለዓለማችን ጠቃሚ ስላልሆነ ከምድር ልናጠፋዉ እንፈልጋለን፤ የእርሰዎ ሃሳብ ምንድን ነዉ? የሚል ነበር፡፡ እርሳቸዉም ጎጂማ ከሆነ መጥፋት ይኖርበታል፤ ግን ጎጂነቱን አረጋግጣችኋል? ደግሞስ ምንም ሳታስቀሩ ሁሉንም ልታስወግዱ ቆርጣችሁ ተነስታችኋል ? ሲሉ ጠየቛቸዉ፡፡ እነርሱም አዎን ፤ ጥቁር ነገር ለሥልጣኔና ለመልካም ነገር እንደማይስማማ ደርሰንበታል፤ ካጠፋንማ የምናጠፋዉ ሁሉንም ጥቁር ነገር ነዉ አሏቸዉ፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሡም፡- ጥሩ የምትጀምሩትስ ከየት ነዉ፤ ከነጮች አገር ነዉ ወይስ ከጥቁሮች? ይላሉ፡፡ ፈረንጆቹም ሃሳባችንን እየተቀበሉት ነዉ ብለዉ እየተደሰቱ ፤ የምንጀምረዉማ በእኛ ሀገር ካለዉ ጥቁር ነገር ነዉ ሲሉ መለሱላቸዉ፡፡ እንደዚህ ከሆነና ምንም ምን የጥቁርን ትንሿንም ሳትንቁ በሀገራችሁ ካለዉ ማጥፋት የምትጀምሩ ከሆነ እስማማለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ዐይናችሁ ዉስጥ ያለችዉንም ጥቁር ነገር ንቃችሁ መተዉ የለባችሁም፡፡ እንዲያዉም ዋናዉ የሰዉነታችሁ ክፍል ላይ በመሆኗ ከእርሷ መጀመር አለባችሁ አሏቸዉ፡፡ የሚያነጋግሯቸዉ ፈረንጆችም በዚህ ጊዜ ደንገጥ ብለዉ ለካ ጥቁር አስፈላጊ ነገር ነዉ አሉ፡፡ ይህን ከነገሩን በኋላ አባ እንደ ልማዳቸዉ ያለምንም ተጨማሪ ማብራሪያ ዝም አሉ፡፡
እዉነት ለመናገር አባ የሰጡት መልስ እኛንም በደንብ የገባን እየቆየ ነበር፡፡እዉነት ነዉ፤ አንዳንድ ጊዜ የማያስፈልጉና መጥፋት አለባቸዉ የምንላቸዉ ነገሮች ሁሉ በደንብ የምናስተዉላቸዉ ከሆነ የሕይወታችን ብርሃን፣ የሰዉነታችን አስኳል፣ የህልዉናችንም መሠረቶች ሆነዉ ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ዝም ብሎ በችኮላ፣ አዉቄያለሁ በማለትና ተቆርቛሪ በመምሰል ነገር ግን በአብዛኛዉ ለራስ በመስገብገብ፣ እወደድና እደነቅ በማለት የምናነሳዉን ሃሳብ ሁሉ ለመተግበር ከመንደርደራችን በፊት ቆም ብሎ ደጋግሞ ማሰብ ፣ ጉዳቱን ብቻ ሳይሆን ጥቅሙንም መመርመር ተገቢ አይደለም ትላላችሁ? ከእነዚህ ጠያቂዎች እንደምንረዳዉ ጥቁር ነገር በሕይወታቸዉ ምን ያህል ቦታ እንደያዘ እንኳ አላስተዋሉም ነበር፡፡ ሌላዉ ቀርቶ መልካቸዉን ያነጣዉ የጥቁር ነገር (የጨለማ መብዛት ወይም የፀሐይ ማነስ) እንደ ሆነ አልተገነዘቡም፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ እንዳሉት የራስ ቅማል ጠቁሮ የወገብ ወይም በልብስ ተሸሽጎ የሚኖር ቅማል የሚነጣዉ ከፀሐይ ማግኘትና ማጣት የተነሣ ነዉና፡፡ ከላይ ታሪኩን በነገሩን አባት በተገለጸዉ መንገድ በጭፍን ሃሳብ ከሚሰጥባቸዉ ነገሮች አንዱ ምጽዋትን የሚመለከተዉ ነዉ፡፡
ብዙ ጊዜ ተቆርቛሪ ነን ባዮች ( አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ተምረናል የሚሉ እንዳንድ ሰዎችንም ያካትታል) የሀገራችንን ገጽታ ያበላሸዉ ምጽዋት (ልመና)ነዉ፤ በዚህ መስክ የተሰማሩ አጭበርበሪዎችና ቢዝነስ ያደረጉት ሰዎች አሉ፤ ስለዚህ መቅረት አለበት ፤ ሕዝቡም ለለማኝ መስጠት የለበትም እያሉ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ በርግጥም አጭበርባሪዎች በመካከል፣ ቢዝነስ ሰሪዎችም እንዲሁ ሊኖሩ መቻላቸዉ የታመነ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በነጋዴዎች መካከል አጭበርባሪዎች ስላሉ ንግድ ይቅር፤ አያስፈልግም የሚል ሊኖር ይችላል? ዛሬ አጭበርባሪ ያልተሰማራበትስ ምን ነገር ሊኖር ይችላል?በባለ ሥላጣኖች መካከል አጭበርባሪ የለምን?በዳኞች፣ በኣካዉታንቶች፣ በጠበቆች፣ በሃኪሞች፣ በጋዜጠኞች፣ በመምህራን፣ በመኃንዲሶች፣ በአርክቴክቶች፣ በተለያዩ ቴክኒሻኖች፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች(NGO`s)፣በባንከሮች፤በአርቲስቶች፣ በሾፌሮች…መካከል ብዙ አጭበርባሪዎች የሉምን? ሌላዉ ቀርቶ በየ ቤተ እምነቱ ስንት ወሰን የለሺ አጭበርባሪ አለ? በሰባኪዉ፣ በዘማሪዉ፣ በባህታዊዉ፣ በቄሱ ፣በመነኩሴዉ(በራሴ ቤት ብቻ ልናገር ብዬ ነዉ) መካከል እንኳ መች ጠፋና? ለዚያዉም በእነርሱ ስም የሚነግደዉን ትቼ፡፡ ለመሆኑ አሁን አጭበርባሪ ያልገባበት ምን አለ? ትምህርትን ያህል የዕዉቀት በር እንኳ ስንት ሸፍጥ ይሠራበታል? ስንቱስ አጭበርብሮና ጥናቱን እየከፈለ እያሠራ እንደሚመረቅ አንሰማም እንዴ?

‹‹መምሩ አዲስ አባ ተማሪዉ ጠገዴ፣
የዘንድሮ ትምርት ተቀና እንደ ስንዴ፡፡››
(ተቀና- ተሸጠ ማለት ነዉ) እያለ የገጠሩ ሰዉ ሳይቀር ሥነ ቃል የቛጠረበት ትምህርት እንኳን ሰርተፍኬት ለሚባል የእንጀራ ኮረጆ በመሸጡ አይደል እንዴ? በእነዚህና በመሳሰሉት መካከል ሁሉ አጭበርባሪዎች በመኖራቸዉ ይቅሩ፤ አያስፈልጉም የሚል ሊኖር አይችልም፡፡ የሚልም ቢኖር እንደ ጤነኛ የሚቆጠር አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም ችግሮቹ ተወግደዉ እንዴት ጤናማ ባለሙያዎችና የሚጠበቅባቸዉን ሁሉ የሚወጡ ተቛማት ሊኖሩን እንደሚችሉ በዉል ያስባል ያሳስባልም እነጂ፤ ለዚያዉም ራሱም ጤነኛ ከሆነ፡፡ ካልሆነም ማሰቡ ችግር የለዉም ፤ ከራስ መጀመር ነዉ ዋናዉ፡፡ ምጽዋትም ከዚህ በተለየ መንገድ ሊታይ አይገባዉም፡፡ ትልቁን ጉዳይ መራብን መቸገርንና አማራጭ ማጣትን ሳያዩ ሰዎቹ የወሰዱትን አማራጭ ( ልመና) እና ማኅበረሰቡ የሚሰጠዉን ምላሽ (ምጽዋት) ላይ በጭፍኑ ለዉግዘት መረባረብ ፡- ተምሬያለሁ፣ ሀገራዊ፣ ሞራላዊና ማኅበረሰባዊ ኃላፊነት አለብኝ ከሚል ቀርቶ ከማናም የሚጠበቅ አይመስለኝም፡፡ ችግሩ በተሻለ መንገድ አይፈታ የሚል ሃሳብ ግን እኔም የለኝም፤ በተማረ ሰዉ ኃላፊነትና የመንገድ ላይ ልመናን በሚያስቀር መንገድ እንፍታዉ ማለት ተገቢ ነዉና፡፡ የሚጠበቀዉም ይሄዉ ነዉ፤ ከሌላዉ ሁሉ የተሻለዉ ምጽዋትም ይሄዉ ነዉና፡፡ ምክንያቱም ዓይነቱ፣ መንገዱና የአፈጻጸም ሥርዓቱ ይለያይ እንጂ ያለ ምጽዋት የሚኖር ሀገርም፣ ሕዝብም፣ ግለሰብም፣ ማኅበረሰብም የለምና፡፡
የተፈጥሮ ትልቁ ሚዛን (balance) የሚጠበቀዉም በመስጠትና በመቀበል ሥርዓት(በምጽዋት)ነዉ፡፡ ሰዉ ከዕፅዋት ኦክስጂን ይቀበላል፤ በምትኩም ካርቦንዳይ ኦክሳይድ ይሰጣል፡፡ በዚህ ሚዛን መጠበቅም ብዙ ሺህ ዓመታትን በሰላም ኖርን፡፡ አሁን ግን ሰዉ ራሱ እየበዛ ካርቦንዳይኦክሳይድ ሰጪ ተቛማቱንም እያበረከተ ዕፅዋትን ግን እያጠፋ ሲሄድ ካርቦናዳይኦክሳይዳችን የሚቀበለን በሚያስፈልገንም መጠን ኦክስጂን የሚሰጠን በመጥፋቱ የተፈጥሮ ሚዛናችን ተዛባ፤ መከራችንም አበዛነዉ፡፡ ምክንያቱም የተፈጥሮ የመስጠትና የመቀበል ሚዛን ስለተዛባ፡፡ የእኛ ቤተ ክርሰቲያን ሊቃዉንትም እግዚአብሔር ዓለሙን በስድስት ቀን ፈጥሮ ከዚያ በኋላ በቃል ኪዳን አጸናዉ የሚሉት ለዚህ ነዉ፡፡ ይህም ማለት በየዓመቱ እግዚአብሔር ይህን ያህል ሰዎች አሉኝ ይህን የሚያክል ሜትሪክ ቶን ኦክስጂን፣ ለዚህን ያክል ዕፅዋት ደግሞ ይህን የሚያክል ሜትሪክ ቶን ካርቦንዳይኦክሳይድ፣ ወዘተ እያለ አያቅድም፡፡ አንድ ጊዜ በሥነ ፍጥረት የሚያስፈልገዉን ከፈጠረ በኋላ ቀሪዉን በመስጠትና በመቀበል ቃል ኪዳን አጸናዉ ማለት ይህ ነዉ፡፡ ምክንያቱም ይህ የአየር መስጠትና መቀበል የሚከወነዉ ማንም ሳይንቲስት ወይም ሌላ ፍጡር ይህ ያስፈልጋል በማለቱ አይደለም፤ የሰዉ የተቃጠለ አየር ለአትክልቱ፣ የእነርሱ የተቃጠለ አየር(ኦክስጂንም) ለሰዉ የሆነዉም ሁለቱ ተቀምጠዉና ተፈራርመዉም አይደለም፤ በእርሱ ቃል ኪዳን ነዉ እንጂ፡፡ ይሄ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን አይደለም የሚል ካለ ካርቦንዳይኦክሳይዴን አልሰጥም ብሎ ዝም ይበልና ይሞክራት፤ ያችን ሳይሰጥ(ሳያሰወጣ) ማስገባቱን እናያለና፡፡ ስለዚህ ከምንተነፍሰዉ አየር ጀምሮ ኑሮአችን የተቀመረዉ በመስጠትና በመቀበል ነዉ ማለት ነዉ፡፡ ከዚህ መለስ ባለዉ ሕይወታችን ሁሉ የበለጸጉ ከምንላቸዉ ሀገሮች ጀምሮ ከመንግሥታትም፣ ከሀብታሞችም፣ ከምሁራንም፣…እስኪ የማይቀበል ማን አለ? ሳይሰጥ የሚቀበልስ? ማንም ሊኖር አይችልም፡፡ ባይሆን በምንሰጠዉና በምንቀበለዉ መካከል በዓይነቱ መጠኑ ሊለያይ ይችላል፡፡ልክ እንደ አየሩ፤ ብዙ ንጹሕ አየር የምናገኘዉ ከትልልቅ ዛፎች ሳይሆን ከትንንሾቹና ከሳሮች እንደሆነዉ ሁሉ፡፡
የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎች እንደሚሉትም ምን ጊዜም ጠቃሚ ኃይል የሚፈጠረዉ በየመሆን አቅም ልዩነት(potential difference) መኖር ብቻ ሳይሆን ፖቴንሻል ከትልቁ ወደ ትንሹ መፍሰስ ሲጀምር ብቻ ነዉ፡፡ ስለዚህ ዓለም ሚዛኗን ጠብቃ የሰዉ ዘር በሰላም ይኖርባት ዘንድ ይህ ከብዙ ወደ ትንሹ ፣ካለዉ ወደ ሌለዉ መፍሰሱ ተፈጥሮአዊና የማይቀር ነዉ ማለት ነዉ፡፡ስለዚህ ክርክሩ ወይም መነጋገሪያዉ የመስጫ ዘዴዉ ላይ ብቻ መሆን ይገባዉ ነበር፡፡ ሃይማኖዊ ምጽዋቱም ዓላማዉ ይሄዉ ብቻ ነዉ፡፡ገንዘቡ ከአለዉ ወደ ሌለዉ እንደሚፈሰዉ የእግዚአብሔር በረከትም እነዲሁ ይፈስስለታል፡፡
በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንም ምጽዋት ሁለት ታላላቅ የመስጠትና የመቀበል ጥቅሞችን የያዘ ነዉ፡፡ የመጀመሪያዉ ሰብአዊ ጠቀሜታ ነዉ፡፡ በየትኛዉም ማኅበረሰብ ዉስጥ በተለያየ ምክንያት መሥራት የማይችሉ ሰዎች ይኖራሉ፤ አሉም፡፡ ባይሠሩም ምግብ ግን ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሌላዉም አይመገቡ ሊል አይገባዉም፡፡ በርግጥ ኮሚኒስቶች ሥራን እናስከብራለን ብለዉ‹‹የማይሠራ አይብላ›› ይሉ ነበር ይባላል፡፡ ይህ ግን ሥራን አያስከብረዉም፡፡ ምክንያቱም ሰዉ መሥራት እየፈለገም በሕመም፣ በዕድሜና(አረጋዊያንና ሕፃናት) በተለያዩ ምክንያቶች ላይሠራ ስለሚችል ‹‹የማይሠራ አያብላ›› የሚለዉ የኮሚኒስቶች መፈክር ሊተገበር የሚችል አይደለም፡፡ እንደኔ ግምት ሀሳቡን ከመጽሐፍ ቅዱስ ነበር የወሰዱት፤ ነገር ግን በትክክል ካለ መኮረጂ ወይም እናሻሽል ከማለት የተበላሸባቸዉ ይመስለኛል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለዉ ‹‹ሊሠራ የማይወድ አይብላ›› /2ኛ ተሰ 3፣10/ነዉ፡፡ ምክንያቱም አሁን በእኛ ሀገር እንደሚታየዉ ሥራ ያለዉ (የተቀጠረ፣ ሰዓት ቆጥሮ የሚፈርም፣ ለመብላት ሲል መሥሪያ ቤት የሚዉል) ነገር ግን መሥራት የማይፈልግ ሺህ ሰነፍ አለ፡፡ መጽሐፋችን አይብላ ብሎ የሚከለክለዉ እንዲህ ያለዉን አስቸጋሪ ሰነፍ ነዉ፡፡ጠቡም ከስንፍና ጋር እንጂ ከሰዉ ጋር አይደለም፡፡ስለዚህ ከላይ በተገለጹትም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች መሥራት ለማይቻላቸዉ ሰዎች መመጽዎት ከማንኛዉም ሰብአዊ ፍጡር የሚጠበቅ ተግባር ነዉ፡፡ በዚህም ሰዉ ለወገናቸዉ ሁሉ ጠንክረዉ ከሚረዱ ከእንስሳትና ከአራዊት እንኳ የማያንስ ፍጥረት ይሆናል እንጂ ልዩ ፍጡር ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ሰብአዊነት በየትኛዉም ሀገር ሰዎችን መኖር የሚያስችል ገንዘብ በመስጠት የሚፈጸም አለም አቀፋዊ ሰብአዊ መብት ሆኖአል፡፡ በየትኛዉም ሀገርም የሚመጸወቱት ሰዎች አሉ፡፡ምጽዋቱ የሚሰበሰበዉም ከሚሠራዉ ሕዝብ ቢሆንም የሚሰበሰብበት ሥርዓት ግን ግብር(tax) ይባላል፡፡ ይህን በማድረጋችንና ወገናችን ከችግርና ከረሀብ ተላቅቆ በማደሩም እርካታንና ሰላምን እናገኛለን፤ ለእኛም የኑሮ ዋስትና ይሆነናል፡፡ በዚህ መሠረታዊ ምክንያት አንድ ኦርቶዶክሳዊ ለአንድ የተቸገረ ሰዉ ሃይማኖቱን ወይም ምግባረ ብልሹነቱን ሳያይ መመጽወት ይኖርበታል፤ የሚመጸዉተዉ ለሰዎቹ እንጂ ለሃይማኖታቸዉ ወይም ለምግባራቸዉ አይደለምና፡፡በሌላ በኩል ቢያንስ የመኖር መብትን የማያስቀር የሀብት መከፋፈያ መንገድ ነዉ ማለት ነዉ፡፡
ሁለተኛዉና መሠረታዊ ጥቅሙ ደግሞ በሰማይ የምንቀበለዉ ጽድቅ ነዉ፡፡ በርግጥ ጽድቁ የሚወሰነዉ በቀዳሚነት በምንሰጥበት የእምነት መጠንና በበጎ ርኅራኄያችን ላይ እንጂ በምንሰጠዉ የገንዘብ መጠን አይደለም፡፡ እነደዚህ ቢሆን ኖሮ ጽድቅ ምንም ምግባር ሃይማኖት ለሌላቸዉ ባለጸጎች የተሸጠች በመሰለን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ምጽዋት መስጠትና መቀበል ነዉ ብለናልና የሰጠ ሁሉ ሳይቀበል አይቀርም፡፡ ‹‹ለሌሎች ዕረፍት ለእናንተም መከራ እንዲሆን አይደለም፣ ትክክል እንዲሆን ነዉ እንጂ፤ የእነርሱ ትርፍ ደግሞ የእናንተን ጉድለት እንዲሞላ በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጉድለት ይሙላ››/2ኛ ቆሮ 8፣14/ ተብሎ እንደተጻፈ በዚህ እኛ ከመጸወትን በሰማይም በምድርም እንመጸወታለን፡፡ ጌታም ዳግመኛ ሲመጣ የሚጠይቀን በዚህ ምድር ምን ሰጠህ ብሎ ነዉ፡፡/ማቴ 25፣33/ በዚህ የማይሰጥ በዚያ ከእግዚአብሔር ምንም በጎ ነገር ሊቀበል አይችልም፡፡ስለዚህ እንመጽዉት፤ ካለእርሱ የምንኖር አይደለንምና፡፡ ትልቁ የዓለማችን የተፈጥሮ ይልቁንም ለሰዉ ዘር እጅግ ጠቃሚዉ የሰላምና የማኅበረሰብ ሚዛን ምጽዋት ነዉ፡፡ እዉነተኛ የሀብት ማከፋፈያ መንገድ ቢኖርና ሰዎች ያለስግብግብነት ቢጠቀሙበት ኖሮ ይህ ሁሉ ጦርነት ለምን ይፈጠር ነበር? ምጽዋት ፍትሓዊ በሆነ መንገድ ዓለማቀፋዊ ሥርዓት ይዛ ስግብግብነትን ገትታ ተተግብራ ቢሆን ዓለም የጸጥታ ዋስትና ታገኝ ነበር፡፡ ግን በየት በኩል?

No comments:

Post a Comment